ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን፣ ኤልፎራና ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለተቋቋመው የዜግነት ኮሚቴ ከፍተኛ እርዳታ አደረጉ
በወቅቱ የሀገራችን ሁኔታ ሕብረተሰቡን ለከፍተኛ ስጋት የዳረገውን የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ስርጭት ለመግታት ሕብረተሰቡ በየዘርፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ለቀረበው ሀገር አቀፍ ጥሪ እየተሰጠ ባለው አፋጣኝ ምላሽ በኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት የተሰማሩት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባላት #ሚድሮክ_ወርቅ_ማዕድን ኩባንያ፣ #ኤልፎራ_አግሮ_ኢንዱስትሪ ና #ዩኒቲ_ዩኒቨርስቲ በጥምረት በክልሉ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለተቋቋመው የዜግነት ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ከፍተኛ እርዳታ አበርክተዋል፡፡
ድርጅቶቹ በገንዘብ መዋጮ 5 ሚሊዮን ብር ሲለግሱ በዓይነት ደግሞ ከቢሾፍቱ የኤልፎራ መጋዘን 1000 (አንድ ሺህ) ኩንታል በቆሎ ያበረከቱ ሲሆን በተጨማሪም ዘርፈ ብዙ በሆነው የችግሩ መቋቋሚያ መንገዶች ውስጥ እገዛ ለማበርከት በተዘረጋው የቁርጠኝነት ፕሮግራም፣ የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን በሻኪሶ ከተማ የሚገኘውን የእንግዳ ማረፊያ በአካባቢው ለሚከሰት የኮቪድ-19 የህክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች በጊዜያዊነት እንዲጠቀሙበት ሲፈቅድ፣ በተመሳሳይም ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በቡራዩ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚገኘው ቅርንጫፍ ካምፓስ ያሉትን የመማሪያ ክፍሎች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁኔታዎች እስከሚስተካከሉ ድረስ ለዚሁ ተግባር አገልግሎት ላይ እንዲውል ተሰጥቷል፡፡
በዛሬው ዕለት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት በተከናወነው ስነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን፣ ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪና ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ያበረከቱትን እነዚህን ከፍተኛ ስጦታዎች በቼክና በማረጋገጫ ደብዳቤ ለክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያስረከቡት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር፣ የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅና የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ናቸው፡፡